15/10/2026
‹‹ጥቅምት 5›› የጻድቅ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዕረፍት (የለውጥ) በዓል ነው።
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ (ግብጽ) ሲሆን፣ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። ወላጆቻቸው ለ30 ዓመታት ልጅ አጥተው ካዘኑ በኋላ በጸሎታቸው ተሰጥተዋቸዋል።
መጋቢት 29 ተፀንሰው ታኅሣሥ 29 ተወለዱ። ገና ሲወለዱም ተነስተው «ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ...» እያሉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
ምድራዊ መብል መጠጥ ሳይመገቡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መላእክትን መስለዋል። በኢትዮጵያም 262 ዓመታትን ጨምሮ በድምሩ 562 ዓመታት ኖረዋል።
የጻድቁ ዕረፍታቸው መጋቢት 5 ቢሆንም፣ በዚያ ወቅት የታላቁ ዓብይ ጾም ስለሚሆን (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 መሠረት በጾም ወቅት የሰንበት በዓላት እንጂ የጻድቃን መታሰቢያ በዓላት በደመቀ ሁኔታ ስለማይከበሩ እና የሐዘን ወቅት በመሆኑ) በዓሉ ወደ ጥቅምት 5 ቀን እንዲዘዋወር ተደርጓል። (እንዲሁም መጋቢት 27 የነበረው የስቅለት መታሰቢያም ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሯል)።
የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃልኪዳንና ጸሎት ከእኛ ጋር ይሁን፤ ከክፉ መከራም ይጠብቀን!