11/02/2026
ዜለንስኪ ቢደውልልኝ ስልኩን አነሳለሁ – ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በስልክ ቢደውሉላቸው ምላሽ እንደሚሰጡ የክሬምሊን አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ ገለጹ። ፑቲን ከውይይት ሸሽተው እንደማያውቁም ተናግረዋል።
መግለጫው የሩሲያና ዩክሬን የሰላም ድርድር በአሜሪካ አስታራቂነት በዚህ ወር በአቡ ዳቢ እንደገና ሊጀመር በተዘጋጀበት ወቅት የተሰጠ ነው።
ሁለቱ መሪዎች ሩሲያ በ2022 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ በቀጥታ ተነጋግረው አያውቁም። የዩክሬን መንግሥት በአካል እንዲገናኙ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ክሬምሊን በስልክ ውይይት እንዲያደርጉ እየገፋ መሆኑ ተዘግቧል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ፑቲን ከዜለንስኪ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ “እስካሁን ማንም አልደወለም” ብለዋል።
በተያያዘ ሩሲያ በሰላም ድርድሩ አውሮፓን ማካተት እንደምትፈልግ ሲገልጽ፣ የዲፕሎማሲ ምንጮች ግን የሞስኮ ዓላማ በኔቶ መስፋፋት ላይ ቅናሽ ለማግኘት እንደሆነ ለቴሌግራፍ ጋዜጣ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት የኔቶ አባል አገራት ሩሲያን በተመለከተ የሚሰጧቸውን ጠንካራ መግለጫዎች እንዲያለዝቡ ጫና ማድረጉን ሮይተርስ የዲፕሎማሲ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት በዘገባው ላይ አስተያየት አልሰጠም።